የዛሬ 30 ዓመት ገደማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሒሣብ መዝገበ አያያዝ ትምሐርት አስተምር ነበር። ዛሬም በሱው ነው እንጀራዬን በስደት ዓለም ከስቃይ ጋር እንደወጥ እያጣቀስኩ የምበላው። ታዲያ ያኔ፣ የመምሕራን ካፌቴሪያ ለምሳ በየጠረጴዛው ዙሪያ በቡድን በቡድን እየተሰበሰብን አንዳንድ ክፍል ውስጥ ያጋጠሙን ገጠመኞች እያነሳን እንስቅ ነበር። አንድ ዕውቅ የኢኮኖሚክስ መምሕር ነበሩ። እግዚአብሔር ይመስገንና፣ ዛሬም በሕይወት አሉ። ስማቸውን ግን አልጠቅስም። [...]
↧